መጋቢት 30/15 (ዋልታ) የክልል ልዩ ኃይልን መልሶ የማደራጀት ተግባር አሁን የተጀመረ ተግባር አይደለም ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
ጄኔራል አበባው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ “የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር አሁን የተጀመረ ተግባር አይደለም፤ ለረጅም ጊዜም ጥናት የተደረገበት ነው” ብለዋል።
ጥናቱ የክልሎች ልዩ ኃይሎች ጥንካሬ ምንድነው ብሎ የተመለከተ ሲሆን፣ የክልሎች ልዩ ኃይሎች ክልላቸውን መጠበቃቸው፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሕይወታቸውን አሳልፈው መስጠታቸው እና መሞታቸው እንዲሁም መቁሰላቸውን በጥንካሬ ተመልክቷል ነው ያሉት።
ነገር ግን የልዩ ኃይል አወቃቀሩ ጉድለት እንደነበረው እና ሕጋዊም እንዳልነበረም አመልክተዋል።
“ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንፃር ሲታይ አወቃቀራቸው ሕጋዊ አይደለም፤ ሕገ-መንግሥቱም እውቅና አይሰጣቸውም” ሲሉ ጄኔራል አበባው አስረድተዋል።
ይህ ልዩ ኃይል አገነባቡ ብሔር ተኮር መሆኑን በማንሣት፣ ይህም የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር መሆኑ ጉድለቱ ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን የፖለቲካ መፍቻ መንገድ አበላሽቷል ያሉት ጄኔራል አበባው፣ “በምን አበላሸ ለሚለው በእኛ ሕገ-መንግሥት ፖለቲካ እና ጉልበት አብሮ አይሄድም፤ ለዚህም ፖለቲከኛው በሐሳብ ማሸነፍ ሲያቅተው ሌላ በትር አለው ማለት ነው፤ የታጠቀውን ልዩ ኃይል ያነሣል” ሲሉ ነው ያስረዱት።
“ሌላው ልዩ ኃይል ያለበት እጥረት፣ ለሀገር የሚሞተውን ኃይል መገዳደር መቻሉ ነው፤ ተገዳዳሪ ኃይል ተፈጠረ” በማለት ለዚህም እንደምሳሌ ለሁለት ዓመት የቆየውን የትግራይ ጦርነት አንሥተዋል።
በጥናቱ ይህ የክልሎች ልዩ ኃይል ትክክል አይደለም ከተባለ አራት ዓመት እንደሆነው ነው ያመለከቱት።
“በዚህም ይህንን ኃይል መልሰን እናደራጀው የሚል ውሳኔ ነው እንጂ የተወሰነው ይበተን፤ ትጥቁን እናስፈታው አልተባለም” ብለዋል።
የሚደራጅበትም መንገድ መከላከያ መግባት ያለበት ወደ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ የሚገባው ወደ ፌዴራል እንዲገባ እና መደበኛ ፖሊስ መሆን የሚፈልገውም መደበኛ ፖሊስ እንዲሆን ነው የተቀመጠው ሲሉ አብራርተዋል።
ይህም ክብሩን፣ ሞራሉን እና ጥቅሙን በማይነካ መልኩ እንደሚፈፀም የተያዘው መርሐ ግብር ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
“ይህም ምንም ክፋት የለውም፤ ሕግ የማስያዝ ነው፤ ጊዜ የሰጠነውም ሌላ ችግር ስለነበረ ነው” ብለዋል።
ሁሉም ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ ጥናቱ ላይ ለረጅም ጊዜ ምክክር ተደርጎ የተወሰነ መሆኑንም አንሥተዋል።
ይህንን ጥናት ሊያስፈፅም የሚችል ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋም አለበት ተብሎ መቋቋሙን በማከልም፣ ይህም የተደረገው አፈፃፀም ላይ ጉድለት እንዳይኖር በማሰብ መሆኑን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።