ልዩ ኃይልን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

መጋቢት 30/2015 (ዋልታ) የክልል ልዩ ኃይልን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
የክልል ልዩ ኃይልን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀ የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ የሀገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ውይይት አካሂደዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።
በዚህም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየሰራ ባለው ጠንካራ ፖሊሳዊ ሥራ ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመለሳል ያሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኢታማጆር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች በየክልላቸው የደረሱበትን መግባባት አድንቀው የሚነሱ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስታዳርድ መሰረት በውይይት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አያይዘውም ወደ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀሉ የክልል ልዩ ኃይል አባላት ጥቅማቸው ተጠብቆ በክብር እንደሚቀበሏቸው ገልፀው በጡረታና በቦርድ በክብር የሚሰናበቱ አባላት መብታቸው እንደሚጠበቅላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የክልል ልዩ ኃይሎች ለሀገር የከፈሉት ውለታ ሳይዘነጋ የልዩ ኃይል አባላቱ በሀገር መከላከያና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ከነ-ሙሉ ጥቅምና ክብራቸው ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚቀበሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተዘጋጀው ስታንዳርድ መሠረት ሬንጀር የደንብ ልብስ የሚጠቀሙት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብቻ መሆኑን አስታውሰው የክልል መደበኛ ፖሊስ ደግሞ ወጥ የሥራ የደንብ ልብስ እንደሚለብስ ገልፀዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታትም የኢትዮጵያ ፖሊስ ከአፍሪካ ምርጥ የፖሊስ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት አንዱ የማድረግ ራዕዩን ማሳካት አለብን ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በማስፈፀሚያ ዕቅዱ የክልል ልዩ ኃይል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ የተወሰነው ከለውጡ በፊት መሆኑን አንስተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስለነበሩ ተግባራዊነቱ ዘግይቷል ብለዋል።
አደረጃጀቱ የዓለም ዓቀፍ፣ የአህጉርና የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ ሁለቱ የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በቀረበው ማስፈፀሚያ ዕቅድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገው የተጀመረውን አደረጃጀት በተቀመጠው አጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ መስማማታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡