የኮቪድ -19 መከላከያ እርምጃዎች እና የህግ ተጠያቂነት የተከለከሉ ተግባራት

• ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት የተከለከለ ነው፡፡
• ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
• እድሜያቸው ከ5 አመት በታች ከሆኑ ህፃናት ወይም በጤና ችግር ምክንያት ለመጠቀም የማይችሉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ከቤት ውጭ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፡፡
• በማንኛውም መንግስታዊ እና ግል ተቋም ሰራተኞችና ተገልጋዮች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም እንዲያገኙ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
• በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ወይም ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ የተከለከለ ነው፡፡
• ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ የመንግስታዊም እና የግል ተቋም፤ ማንኛውም ፋብሪካ፤ ሆቴል፣ አስጎብኚነት እና ሌሎችም የቱሪዝም መስክ፤ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አሰሪዎች፤ ማንኛውም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ወይም ተቋም አካላዊ ርቀት መጠበቁን፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች እንደ ዘርፉ ባህሪ አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡
በቀብር ስነ ስርዓት፣ በስብሰባ ወቅት፣ የሃይማኖት ስነ ስርዓቶች ሲፈፀም እና መዝናኛ ቦታዎች ወቅት መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄ እርምጃዎች
• በቀብር ስነ ስርዓት፣ በስብሰባ ወቅት፣ የሃይማኖት ስነ ስርዓቶች ሲፈፀሙ እና መዝናኛ ቦታዎች የሚከተሉት ጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ እንደሚገባ መመሪያው ይደነግጋል፡፡
• የቀብር ስነ ስርዓትን በተመለከተ፡- የቀብር ስነ ስርዓት አፈጻጸም በአጠቃላይ ከ50 ሰው መመብለጥ የለበትም፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማድረግና ሁለት የአዋቂ እርምጃ በመራራቅ መከናወን አለበት፣ ከቀብር በኋላ ለቅሶ ለመቀመጥ ከ50 ሰው መብልጥ የለበትም፡፡
• ስብሰባን በተመለከተ፡- በተቻለ መጠን በኦንላይን አማራጮች ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ማድረግ፣ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ50 ሰው በላይ መሆን የሌለበት ሲሆን ከዛ በላይ መሰብሰብ የግድ ከሆነ ለሰላም ሚኒስቴር (ለክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ) በማሳወቅ መሰብሰቢያ ቦታው መያዝ ከሚችለው በ¼ ሰው ማድረግ ይቻላል፣ በተሳታፊዎች መሃል ሁለት የአዋቂ እርምጃ ያህል (2 ሜትር) ለመጠበቅ በሚያስችል አዳራሽ መካሄድ አለበት፣ የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር) እና ዉሃ በበቂ መዘጋጀት አለበት፡፡
• አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ካፌዎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የመዝናኛ እና መጫዎቻ አገልግሎት የሚሰጡ ስፍራዎች በተመለከተ፡- በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ሰው በላይ ማስተናገድ የተከለከለ ነዉ፤ በእያንዳንዱ ጠረጴዛ መካከል የሁለት ሜትር ርቀት ሊጠበቅ ይገባል፣ አገልግሎትን የሚሰጡ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፣ ከመስተንግዶዉ ዉጭ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡
• የሀይማኖት ስነ ስርዓትን በተመለከተ፡- ሀይማኖታዊ ስርዓት ከሁለት የአዋቂ እርምጃዎች ተረራርቆ መፈጸም አለበት፣ ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛውን የማይበልጥ ሰው በመያዝ ስርዓቱን ማካሄድ ይኖርባቸዋል፣ ማንኛውም ሰው የአፍእና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይደረግ ወደ እምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው፡፡
የተጣሉ ግዴታዎች :-
• የተቋማት ግዴታ- በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የዘርፍ መስርያ ቤቶች በየመስካቸው የሚያጣቸው መመርያዎችና አሰራሮች የኮቪድ 19 በሽታን ለመግታት ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት፣ በዚህ መመርያ ውስጥ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የማይቃረኑና ተጣጥመው የወጡ መሆን አለባቸው፡፡
• የግለሰብ ግዴታ- ኮቪድ 19 በሽታ አለብኝ ብሎ እራሱን የሚጠረጥር ሰው ለሚመለከተው አካል ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለበት፣ የመመርመርና ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ አስፈላጊው ጥንቃቄ የማድረግ ሀላፊነት አለበት፣ በሽታው አለበት ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ስለመኖሩ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለጤና ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአቅራቢያው ለሚገኝ፣ ለሚገኙ የጤና ተቋም ወይም ባለሞያ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡
የህግ ተጠያቂነት:-
• በዚህ መመሪያ የተደነገጉ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው በወንጀል ህግ ድንጋጌዎች መሰረት እንደሚቀጣ መመሪያው ያመላክታል፡፡ ከዚህ አንፃር የወንጀል ህጉ አንቀጽ 522 እና ሌሎች ድንጋጌዎች አግባብነት ያላቸው በመሆኑ ተፈጻሚ ይህን መመሪያ በሚጥሱ ሰዎች ላይ ይሆናሉ፡፡
• የወንጀል ህጉ አንቀጽ 522 /1/ ማንም ሰው በሽታን ለመከላከል በህግ የተቀመጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቦ የጣሰ እንደሆነ እስከ 2 አመት ሊደርስ የሚችል የእስራት ቅጣት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡
• ወንጀሉ በቸልተኛነት የተፈፀመ ከሆነ እስከ 6 ወር የሚደርስ እስራት ቅጣት እንደሚቀጣ በህጉ ተመላክቷል፡፡