ግንቦት 21/2013 (ዋልታ) – ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው አራተኛው ዙር የኮዋሽ/የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን/ፕሮጀክት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በፊንላንድና በክልል መንግሥታት እንደሚሸፈን ተገልጿል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፤ አራተኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል።
ፕሮጀክቱ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም የጠቆሙት ዶክተር ነጋሽ፣ በፕሮጀክቱ ሲዳማ ክልልን ጨምሮ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዙሮች ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በተመረጡ 76 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፣ በአራተኛው ዙር የሲዳማ ክልልን በማካተት በ37 ዞኖች 99 ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ በርካታ ባለ ድርሻ አካላት ቢኖሩም የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል ያሉት ዶክተር ነጋሽ፤ አራተኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮጀክት 60 በመቶው በመንግሥት 40 በመቶው ደግሞ በፊንላንድ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።