የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተቋርጦ የቆየውን የገጽለገጽ ትምህርት ለማስጀመር ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ገለጸ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ1ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እያሰለጠነ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የገጽ ለገጽ የመማር ማስተማር ሂደት አሁን በተለያዩ ቦታዎች መጀመሩ ይታወቃል፡፡ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም የገጽገጽ ትምህርት ለማስጀመር ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጿል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዳይከሰት ቅድመ ጥንቃቄዎች በበቂ ሁኔታ መደረጋቸውን እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲከናወን ውይይት ማድረጉን ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል ተናግረዋል፡፡
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የ2012 ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ዛሬ እያሰመረቀ ነው፡፡
“በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ በሰላም ሚኒስቴር መሪነት የተዘጋጀው የበጎ ፈቃደኝነት ወጣቶች ስልጠና በሀገር አቀፍ ደረጃ በ21 ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል፡፡ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም ከ1ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ዶ/ር ፋሪስ ገልጸዋል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ነባር ተማሪዎችን ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ለመቀበል በዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)