ጳጉሜን 3/2015 (አዲስ ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ጳጉሜን 3 2015 ዓ.ም እየተከበረ የሚገኘውን የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የበዓል ስጦታና ማዕድ አጋራ።
የሚኒስትሩ ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በጎ ተግባራትን ማከናወን ለሀገርና ለትውልድ መልካምነትን ማሳየት በመሆኑ እለቱን በማስመልከት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በተለይም በችግር ላይ ያሉ ህፃናትን መንከባከብ እና መደገፍ ለተወሰነ አካል ብቻ የማይተው የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
በዚህም መሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለህፃናትና በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች ስጦታና የማእድ ማጋራት ማከናወኑን ተናግረዋል።
በሀረሪ ክልል ባለፈው ሳምንት ለ400 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተሰጠው ተልዕኮ በተጓዳኝ ለአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት በማድረግም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም የበጎነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለተቸገሩ ወገኖች የበዓል ሰጦታና የማዕድ ማጋራት አከናውነናል ነው ያሉት።
ለበጎ ተግባሩ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ባዋጡት ገንዘብ ድጋፉ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይነትም አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ጳጉሜን 3 የበጎነት ቀን “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም ተግባራትን በማድረግ በመከበር ላይ ይገኛል።