የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አደረጉ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ገለጻውን ለጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲ፣ ርዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ አምባሳደሮች ነው ያደረጉት።

በገለፃቸው፣ የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ መንግስት በክልሉ የወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ አምባሳደሮቹና የየሃገራቱ መሪዎች ያሳዩትን ድጋፍ አድንቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ እንደ አፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርነቷ በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት የምትጫወተው ሚናም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በገለጻቸው ዘመቻው ንጹሃን ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ እና መንግስት በክልሉ ህግና ስርአትን ለማስፈን የያዘውን እቅድ ማከናወን በሚያስችለው አግባብ በፍጥነት መጠናቀቁንም ለአምባሳደሮቹ አስረድተዋል።

አሁን ላይም መንግስት በክልሉ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችንና የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ የሚያስችሉ አማራጮችን መዘርጋትና ማረጋገጥ እንዲሁም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት በክልሉ ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

አምባሳደሮቹም መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃውን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ በፍጥነት በማጠናቀቁ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም መንግስት ለተጎዱ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቀጠናው “የሰላም መልሕቅ” መሆኗን በመጥቀስም የየሃገራቱ መሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተረጋግጧል፡፡

(ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)