የዓለም ባንክ ለአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የ12 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

ሰኔ 16/2013 (ዋልታ) – የዓለም ባንክ በአፍሪካ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት እጥረት ለመቅረፍ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

ባንኩ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በሚሰራው የትብብር ስራ 4 መቶ ሚሊየን ለሚሆኑ አፍሪካውያን የሚሆን ክትባት የሚገኝበትን መንገድ ለማፈላለግ እና ለስርጭት የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

የዓለም ባንክ ክትባቱን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውል 4 መቶ ሚሊየን የጆንሰን እና ጆንሰን ክትባቶችን በየሀገራቱ ተደራሽ ለማድረግ ጭምር የሚረዳ 12 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚሰጥ የባንኩ የኦፕሬሽን ዲሬክተር አሌክስ ቫን ትሮትስበርግ ተናግረዋል፡፡

ድጋፉም በአፍሪካ ህብረት በተቋቋመው የክትባት አፈላላጊ ግብረ-ሀይል በኩል እንደሚቀርብም ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የዓለም ባንክ ይህን ውሳኔ የወሰነው ከአንድ ቀን በፊት የአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች ከዓለም ባንክ ግሩፕ ጋር አፍሪካ ሶስተኛውን የኮሮና ቫይረስ ማዕበል መከላከል እንድትችል ክትባቱን በፍጥነት ማግኘት በምትችልበት ሁኔታ ላይ ከመከሩ በኋላ እንደሆነም ከባንኩ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመልክታል፡፡

ይህ የዓለም ባንክ ፕሮጀክት የአፍሪካ ህብረት እኤአ በ2022 በአህጉሪቱ ከሚገኙ ሰዎች መካከል 60 በመቶውን ለመከተብ ያስቀመጠውን ግብ ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡