የዓለም ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳዬ


ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) እስራኤል በአራን ላይ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃን ተከትሎ በዓለም የነዳጅ ዋጋ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።

ሰሞኑን በሁለቱ አገራት መካከል እየተባባሳ በመጣው ግጭት ምክንያት በዓለም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር እንደሚችል እየተገለጸ ነው።

በዚህም ብሬንት የተሰኘው የነዳጅ ምርት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በዓለም ገበያ 90 ነጥብ 54 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን ሚንት የተሰኘ የቢዝነስ ነክ መረጃ አቅራቢ ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት መባባስንና የነዳጅ አምራች አገራት ህብረት የሆነው ኦፔክ አቅርቦት ለመቀነስ መወሰኑ ለዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በሌላ በኩል በወርቅ ዋጋ ላይም ጭማሪ መታየቱ የተገለጸ ሲሆን አንድ ወቄት (28.349 ግራም) ወርቅ የ1 በመቶ ጭማሪ በማድረግ በ2 ሺሕ 422 ዶላር እየተሸጠ መሆኑ ተመላክቷል።