የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ክልል በአስገዳጅ ሁኔታ ከታዳጊ እስከ አዛውንት ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ በማጋላጥ ላይ የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም የአሸባሪ ቡድኑ ዳግም ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በተግባራዊ እርምጃዎቿ እያሳየች መሆኗን ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘበው የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣  ሰብዓዊ ዓላማ ያለው የተኩስ ማቆም መደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ በመንግሥት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችና ሌሎችም ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

መንግሥት አሁንም ለሰላም ያለውን አቋም የሚያሳዩ ግልፅ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለተለያዩ የዓለም ማኅበረሰብ አካላት የማስረዳቱ ሥራ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ሆኖም ኢትዮጵያ ለሰላም በርካታ ርቀቶችን ብትጓዝም አሸባሪው ሕወሓት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን የሕወሓትን የዳግም ጦርነት ዝግጅትና የታጣቂ ምልመላ በትክክል ተገንዝቦ በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW