መጋቢት 20/2016 (አዲስ ዋልታ) በጋምቤላ ክልል የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማሻከር የሚሰሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን ለመንግስት አጋልጦ በመስጠት ረገድ ህብረተሰቡ ትብብሩን እንዲያጠናክር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ የዜጎች በሰላም የመኖር ዋስትናና የህግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርብ የመንግስት ኃላፊነት ነው ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋትና የዜጎችን የሰላም ዋስትና ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አስከባሪ አካላት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የሰዎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚገቱ ችግሮች አስቸኳይ እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባም መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ሰላም እንዳይኖር የሰው ህይወት እንዲጠፋ ንብረት እንዲወድምና የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገደብ በሚያደርጉ አካላት ላይ አስቸኳይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባም ተናግረዋል።