የፈረንሳይ መንግስት ለክልሉ ልማቶች የሚያደርገው ድጋፍ የሚበረታታ ነው – ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ


መጋቢት 19 /2016 (አዲስ ዋልታ) የፈረንሳይ መንግስት በአማራ ክልል ለሚካሄዱ የቱሪዝም፣ የጤናና ሌሎች ልማቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ጋር በልማትና ድጋፍ ዙሪያ በባህርዳር ከተማ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይም ርዕሰ መስተዳድሩ የፈረንሳይ መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገናን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረገ ያለውን የትብብር ድጋፍ አመስግነዋል።

በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ለተጎዱ ወገኖች በፈረንሳይ መንግስት እየተደረገ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ በበኩላቸው በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ምርጥ ዘር በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚደግፉ ተናግረዋል። ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በቅርስ ጥገና፣ በጤናና ሌሎች የልማት መስኮች ያደርጉት የነበረውን ድጋፍ ለማስፋት መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።