የደራሼዎች ፊላ ሙዚቃ

#ሀገሬ

የደራሼ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ ነው፡፡ ፊላ ሙዚቃ የደራሼ ብሔረሰብ ጥንት ሀገረ ሰብ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው ከቀርቀሃና ከሸምበቆ የሠሩት የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ የፊላ ሙዚቃ የክብር ሙዚቃም ነው፡፡ ጥንታዊ አጀማመሩ እጅግ ለተከበሩ ለጎሳ መሪያቸው ወይም ለንጉሳቸው ይቀርብ እንደነበር ይነገራል፡፡

የፊላ ሙዚቃ መሳሪያ 24 ዓይነት የተለያዩ ቀለም ወይም ቃና ያላቸው ድምፆችን ያወጣል። የድምፆች ቀለማት በሦስት ምድብ የሚከፈሉ ሲሆን ወፍራም መካከለኛ እና ቀጭን ድምፅ በመባል ይመደባል።

በብሔረሰቡ ካሳኒታ የሚባለው ወፍራም ደምፅ ቀለም ያለውና ቤዝን የሚወክል ነው። ታለቅ የሚል ትርጉምም አለው። መካከለኛ የድምጽ ቀለም ያለው ደግሞ ኦዳንዲያ ይባላል 3ኛው የድምጽ ምድብ ቀጭን ወይም አነስ ያለ ድምጽ ሲሆን ፍትንፊታያ ይባላል፡፡ እነዚህ ሶስት ቀለማት ያላቸው ድምፆች እያንዳንዳቸው 8 ዓይነት የተለያዩ ድምጾችን ያወጣሉ፡፡

የፊላ ትክክለኛውን ድምፅና ዜማ ለማምጣት የቀርቀሃና የሸምበቆ ዓይነት ከመምረጥ ይጀምራል፡፡

ታዲያ ወፍራም ድምጽን ከመካከለኛው እንዲሁም ቀጭን እያሉ አንደኛውን ከሌላኛው ድምጽ የመለየት ችሎታ ያላቸው ጥበበኞች ባህላዊውን ሙዝቃ መሣሪያ ከቀርቀሃና ከሸምበቆ ይሠሩታል። እነዚህ ሰዎች ድምጽን የመለየት ችሎታቸው የተለየና ለድምጽ ያላቸው ቅርበት ከፍተኛ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

በዘህ ረቂቅ ጥበብ ታጀበው በተሠሩ ፊላዎች ከ20 እስከ 40 ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡ ፊላ በፆታ ያልተገደበና አሳታፊ እንዲሁም የትንፋሽ ሙዝቃንና ውዝዋዜን አንድ ላይ የሚጠቀም በመሆኑ የፊላ ጫወታ ተብሎም ይጠራል። ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች አብረው በህብረት ይጫወታሉ፡፡

ከጨዋታው ባሻገርም በህብረት ውስጥ ከፍ ያለ ነገር መኖሩን በተግባር የሚተነትን ፍልስፍናም አለው ፊላ። የትንፈሽ ሙዚቃ መሣሪያ በመሆኑም ከእያንዳንዱን 24 ሰው ትንፋሽ የሚፈልግ በህብር ሲጫወቱ ደግሞ ቀለም ያለው ድምፅና ዜማን የሚያወጣ ነው። በኬሮግራፊ የታከለ የመዝቃ ክንዋኔም አለው፡፡

በ1950ዎቹ አከባቢ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ የመጡ ጥቁር አሜሪካዊያን የጃዝ ሙዚቃን እንደፈጠሩ ይነገራል፡፡ ደራሼዎች ግን የፊላ ሙዚቃን በባህላዊ መንገድ መጫወት የጀመሩት ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት እንደሆነ የብሄረሰቡ አባቶችና ተወላጆች ይናገራሉ።ይህ ደራሼዎች በሀገር በቀል የጥበብ ዕውቀታቸው የፈለሰፉትና ከብዙ ዘመናት በፊት የጀመሩት የፊላ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን መግለጽ የሚችልና አፍሪካ የሙዚቃ ምንጭ ስለመሆኗ ምልክትም ነው፡፡

ቸር እንሰንብት!!

በሠራዊት ሸሎ