በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች አቀባበል ተደረገላቸው

የካቲት 26/2016 (አዲስ ዋልታ) በስኮትላንድ ግላስኮው በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የላቀ ውጤት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት።

ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና የስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ ዳዊት አስፋው፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሻምፒዮናው ከየካቲት 22 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በስኮትላንድ ግላስኮው መካሄዱ ይታወቃል።

በውድድሩ በ13 አትሌቶች የተወከለችው ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅ፣ በአንድ የብርና በአንድ የነሐስ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በ800 ሜትር ሴቶች በፅጌ ዱጉማ እና በ1500 ሜትር በፍሬወይኒ ኃይሉ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

በ3000 ሜትር ሴቶች አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ የብር እንዲሁም በ3000 ሜትር ወንዶች ሰለሞን ባረጋ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

ለአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ የእውቅና መርኃ ግብር እንደሚካሄድም ተገልጿል።