የደቡብ ዕዝ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አካሄደ

ሐምሌ 6/2014 (ዋልታ) የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከአሚባራ ወረዳ መስተዳደር እና ከአቡነ ዮናስ የአረጋውያን ድጋፍ መስጫ ማዕከል ጋር በመተባበር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር አካሄደ።

በአፋር ክልል የአሚባራ ወረዳ አስተዳደር አብዶ አሊ እንደተናገሩት እንደ ሀገር የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማሳካት ሠራዊቱ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የጎላ ነው።

መርኃ ግብሩን ያዘጋጀው የአቡነ ዮናስ አረጋውያን ድጋፍ መስጫ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት እና ሥራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ደበበ መርኃ ግብሩ ለ 1 ወር ያህል የሚቆይ መሆኑን በመግለፅ ሠራዊቱ በልማት ሥራው ላይ ላደረገው ቀና ትብብር አመስግነዋል።

የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ተወካይ ኮሎኔል ሁሴን አስረስ በበኩላቸው ማሰልጠኛው ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የረጅም ጊዜ መልካም ግንኙነት እንዳለው በመግለፅ ሠራዊቱ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ውጥኖች ላይ የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።