የዲጂታል ኢትዮጵያ አተገባበርና አፈፃፀም አውደጥናት ተካሄደ


ነሐሴ 25/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካት ጋር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አተገባበርና አፈፃፀም አውደጥናት ማካሄድ ጀምሯል፡፡

አውደጥናቱ በሦስት አመት የተከናወኑ ተግባራትን መገምገምና በቀሪው ሁለት አመታት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዋናነት የዲጂታል መሰረቶች በማልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የዲጂታል መሰረቶችን ማልማት የአንድ ተቋም ወይም በአንድ ፐሮጀክት አማካኝነት የሚካሄድ አይደለም ያሉት ሚንስትሩ የዲጂታል መሰረቶች ልማት በአላማ በተሳሰሩ በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት የሚለሙ በመሆናቸው ተቋማችን በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እቅድ ትግበራ ኢትዮጵያን የበለጸገች ለማድረግ እና ሁሉን አቀፍ አካታች ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ አስተዋጸኦ ማድረግ የሚችል ትልቅ እርምጃ ነው በለዋል፡፡

ተግባሩ ስኬታማ የሚሆነው ውጤታማ በሆነ መንገድና በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሙሉ ድጋፍ ተግባራዊ ከሆነ ብቻ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአገራችን መረጃን ቀምሮ ለመያዝ እና ለሊሎች ለማጋራት ያለው ውስነነት እና በአንዳንድ ባለድርሻ አካላት ዘንድ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን የኮሚቴውን ስራ በወቅቱ እና በሚፈልገው የጥራት ደረጃ ለማጠናቀቅ እንዳይችል ማድረጉንም አንስተዋል ።

የስትራቴጂው የመጨረሻ ግብ የአገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት በማረጋገጥ አዳዲስ የስራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አገራዊ ገቢን መጨመር እና አካታች የሆነ ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህይወት እንዲሻሻል ማድረግ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ለመቀየር ያስችላል ተብሎ የቀረበ የመንግስት እቅድ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ስትራቲጂው ከሀገሪቱ የልማት ራዕይ የፖሊሲ ዓላማዎች እና የቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ጋር የተሰናስሎ እና በወቅቱ የነበሩ አለም አቀፋዊ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮችን አካቶ እንዲረቅቅ ተደርጎ ሰኔ 8 ቀን 2012 በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁም ይታወሳል ፡፡

በሳራ ስዩም