ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መነቃቃት እየታየበት መሆኑን ገለጸ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአይ ሲቲ ኢቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ዲጂታል ፋይናንስ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ፒ ኤች ዲ) የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ቁልፍ የሆነውን የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ማዘመን ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዘርፉ እንዲነቃቃ የማስፈፀሚያ መመሪያና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስራዎች መሰራታቸውን ነው የተናገሩት።
የብሄራዊ ባንክ የክፍያ ስርዓት ክትትልና ልማት ዋና ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳምጠው እንዳሉት፤ የዲጂታል ክፍያዎችን ለመፈፀም የሚያስችሉ ስርዓቶችን ለመዘርጋት መደላድሎች በመፈጠራቸው ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ ነው።
አሁን እየተሰራበት ያለው የወረቀት ገንዘብ ልውውጥ ባለበት መቀጠል እንደማይቻል ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኦንላይን ክፍያ ለመፈፀም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተደርጓል ያሉት ሃላፊው፤ ከመረጃ መረብ ደህንነት ጋር በተያያዘም ትልቅ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።
የ ኢት ስዊች ዋና ስራ አስፍፃሚ አቶ ይለበስ አዲስ ከአካውንት ወደ አካውንት፣ ወደ ዋሌት እና ወደ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ ማስተላለፍና የኦንላይን ባንኪንግ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አብራርተዋል።
የሞኔታ ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ የምሩ ጫንያለው በአሞሌ ክፍያ በኩል ከ2 ሚሊየን ተጠቃሚ ወደ 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እንደሚዘዋወር አብራርተዋል።
የስፖርት ውድድር መግቢያ ትኬት፣ የትምህርት ቤትና የመዝናኛ ክፍያ በአሞሌ በኩል እንደሚፈፀሙና በቀጣይ ኢ-ኮሜርስና ኢ-ማድረስ (E- delivery) ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የንግድ ባንክ የመረጃ ስርዓት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማረ አሰፋ የዲጂታል ክፍያ ተደራሽነትን ለማስፋትና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አብራርተዋል።
የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን እስከ ገጠር ድረስ ለማውረድና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅሳቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው በውይይቱ ከ250 በላይ የዘርፉ ተዋናዮች እና ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡