“የጁንታው መደምሰስ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት አይነተኛ ሚና አለው” የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

 

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የካቲት 12/2013 ዓ.ም (ዋልታ) የጁንታው መደምሰስ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት አይነተኛ ሚና እንዳለው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጹ፡፡

የሕወሃት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ የእብደት ተግባር መሆኑን የገለጹት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የቡድኑ ዓላማ የሰሜን እዝ ብቻ ሳይሆን የኤርትራ መንግስትንም ለመቀየር ፍላጎት ነበረው ብለዋል፡፡

የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ የሚገደለውን በመግደልና የሚማረከውን በመማረክ ወይም ደግሞ እጁን ሰጥቷል ብሎ ካወጀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መግባት፣ እግረ መንገዳቸወን ከተሳካላቸው ደግሞ አስመራ ያለውን መንግስት ለመቀየር ነበር የሕወሃት ዓላማ ብለዋል አቶ ኢሳያስ፡፡

ሕወሃት የተሳሳተ የጦርነት ቀመር በመውሰድና የቀደመውን አስተሳሰብ ለመጫን በመሞከሩ አሁን ላለበት ደረጃ መድረሱንም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አብራርተዋል፡፡

የሕወሃት ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ዘርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ላይ በማተኮሩ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ እንድትገባ ከፍተኛ ሥራዎች መሥራቱን ገልጸዋል።