መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – የጉጂ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ የሚውል 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መለገሳቸውን የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በገበታ ለሀገር ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም ሰራተኞቹ ተናግረዋል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዳዲ ኩራ እንዳሉት፤ በፕሮጀክቶቹ ድጋፍ ላይ የህዝብ ተሳትፎ ለማነቃቃት ከሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የመንግስት ሰራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች 36 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መገባቱን አስታውሰዋል።
ከዚህም እስካሁን ከመንግስት ሰራተኞች ብቻ የተገኘ ከወር ደመወዛቸው 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ባንክ ገቢ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የነገሌ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ አቶ እያሱ አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲወል በየወሩ የሚቆረጥ ሙሉ የወር ደመወዛቸውን እንደለገሱ ተናግረዋል፡፡
ለሀገር እድገትና ገጽታ ግንባታ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን መደገፍ የውዴታ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ በበኩላቸው ገቢው ለገበታ ለሀገር የሚውል በስምንት ወር ተቆርጦ የሚያልቅ የወር ደመወዛቸውን መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡
የሀገራችን ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ልማትና እድገት ለማፋጠን ሁለነተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ በማድረግ ሁላችንም በትብብር ልንሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡
በገበታ ለሀገር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ከዳር እስኪደርሱ ድረስ አቅም የፈቀደውን ሁሉ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡