የግሉ ዘርፍ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የመሪነት ሚና ሊኖረው ይገባል ተባለ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) የግሉ ዘርፍ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የመሪነት ሚና ሊኖረው እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከግሉ ዘርፍ የቴክኖሎጂ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ያካሄደ ሲሆን ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ የግሉ ዘርፍ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የመሪነት ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ግቡ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ምርታማነትን ማሳደግና ገቢ መጨመር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማስቻል መንግሥት አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በ2014 ዓ.ም የፀደቀውና ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ ፖሊሲ የግሉን ዘርፍ የመሪነት ሚና ማረጋገጥ ዋናው ተግባሩና የትኩረት ማዕከሉ ነው ተብሏል።

ፖሊሲው የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025ን ለመተግበር ከፍተኛ እድል የሚሰጥ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ መርኃ ግብሩ የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ያስችለዋል ነው የተባለው።

ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው በውይይቱ በዘርፉ የተገኙ አዳዲስ እድሎች፣ የቀረቡ አማራጮችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ቀርበው ተመክሮባቸዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW