ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይበልጥ የአፍሪካ አገራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የዓባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲቀየር የበኩሏን ሚና እየተወጣች ትገኛለች።
ግብጽና ሱዳን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን አቋም በመጻረር የግድቡን ጉዳይ ወደማይመለከታቸው አካላት እየወሰዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ችግሩን የሚመለከታቸው አካላት ብቻ እንዲያዩት በማመን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው ጉዳይ ጽኑ አቋም ይዛ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የግድቡ የዲፕሎማሲ ስራ በአፍሪካዊ መፍትሄ ላይ መመስረት እንደሚገባው የጠቀሱት ዶክተር ያዕቆብ፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ነገ ሊደርስባቸው እንደሚችል ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ግድቡን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች አፍሪካ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ምሁራን እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ ግንባታ በሙያቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀው፣ “በቀጣይም ለበለጠ ኃላፊነት ሊዘጋጁ ይገባል” ብለዋል።
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ በራስ አቅም ከድህነት የመውጣት ጥረት መሆኑን በማስገንዘብ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።