የጠላቶቻችንን ሴራ እያከሸፍን የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን – ኦሮሚያ ክልል

ሚያዝያ 24/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጠላቶቻችንን ሴራ እያከሸፍን የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን አለ።
የክልሉ መንግሥት ባወጣው የአቋም መግለጫ የጠላቶቻችንን ሴራ እያከሸፍን የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን ብሏል።
ሀገራችን ለዓመታት የገነባችው የሕዝቦች አብሮ መኖር እሴት በውስጥ እና በውጭ ጠላቶች ለሚሸረቡ ሴራዎች እጅ ሳትሰጥ በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል መከባበር፣ ፍቅርና ወንድማማችነት እያጠናከረች ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር እዚህ ደርሳለች ብሏል የክልሉ መግለጫ።
ክልሉ በመግለጫው ፣ በሰላም ተከባብሮ በሚኖር በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ለዓመታት ሴራ ቢሸረብም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ለመሸርሸርና ነጻነቱን ለመንጠቅ ለሚፍጨረጨሩ ጠላቶቹ እጅ ሳይሰጥ ባህሉን፣ ወጉን፣ ቋንቋውን እና ሃይማኖቱን እያጠበቀ ይገኛል ብሏል።
በሕዝቦች ትግል ከስልጣን የተወገዱት ኃይሎች መልሰው ስልጣን በመያዝ እና ሕዝቡን ለማሰቃየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ብሔርን እና ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ በሰላም አብሮ የሚኖር ሕዝብ መካከል መርዝ የሚረጩ አክራሪ ኃይሎች የጠላቶቻችንን ተልዕኮ ለማሳከት ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ ብሏል መግለጫው።
ብሔርንና ሃይማኖትን ከለላ አድርገው የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ኃይሎች በዛሬው እለት የኢድ አል ፈጥር በዓልን ለማከበር በወጣው የሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ ተደብቀው የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማሳካት በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጥረት በሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች እና በጸጥታ ኃይሎች ቅንጅት ሊከሽፍ መቻሉ ተገልጿል።
የክልሉ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠላቶች ተልዕኮን ይዘው የሚንቀሳቀሱ አክራሪዎች እና አሸባሪዎች ላይ የሕግ የባለይነት የማስከበር ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ገልጾ፣ የክልሉ ሕዝብና ሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጠይቋል።
የሙስሊም ማኅበረሰብ በጥቂት አካላት በተሸረበ ሴራ ሳይረበሽ በዓሉን እንዲያከብር የክልሉ መንግሥት መልዕክት አስተላልፏል።