የጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት

መሪጌታ አብራራው መለሰ

ነሐሴ 25/2013 (ዋልታ) – ታሪካዊው የጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት።

የፈለገ ፀሐይ በቅሎ አግት ጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሦስተኛው ክፍለዘመን እንደተመሰረተ ይገለጻል።

የጨጨሆ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል ገዳም ገንዘብ ያዥ የሆኑት መሪጌታ አብራራው መለሰ ትናንት ምሽት አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በከባድ መሳሪያ ጥቃት ቤተክርስቲያኑን ማውደሙን ተናግረዋል።

መሪጌታ አብራራው የሽብር ቡድኑ በእምነት ተቋማት ላይ ይህን መሰል ውድመት ማካሄዱ ለጸረ ሕዝባዊነቱ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸው፣ “እያጠፋናችሁ ነው የምንሄደው ብለው ነበር፤ እንዳሉትም አድርገዋል” ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ባደረሰው የከባድ መሳሪያ ጥቃት የቤተክርስቲያኑ 14 መስኮቶች፣ 5 በራፎች፣ ሕንጻውና ጣሪያው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።

መሪጌታ አብራራው የሽብር ቡድኑ በግቢው ውስጥ የሚገኙ ዕጽዋትንም እንዳወደመ ተናግረው፣ የገዳሙ ፍልፍል ዋሻም በአሸባሪ ቡድኑ መፍረሱን ጠቁመዋል።

ቤተክርስቲያኑ ወደነበረበት እንዲመለስ ርብርብ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

“በአካባቢው ሆነው ቤተክርስቲያኑን ያስመቱ ግለሰቦችም በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ማለታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።