የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መጠናቀቁ ተገለጸ

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መጠናቀቅን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ከዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ድምፅ መስጫ እለት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ምንም አይነት ቅስቀሳ ማድረግ የማይችሉ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢንተርኔት፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በግንባር፣ ቤት ለቤት፣ በአደባባይ ፣ በአዳራሽ ስብሰባ ምንም አይነት ቅስቀሳ ማከናወን በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ተገልጿል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ቃለ መጠይቆችን ማድረግ አይፈቀድላቸውም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ 148 የክልልና የፓርላማ ግል እጩዎች በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የግል እጩ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ታምኖበት ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑንም ተጠቁሟል፡፡

ከደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ህዝበ ውሳኔ ጋር በተገናኘ የተቀየረ ነገር አለመኖሩን የገለፁት ኮምዩኒኬሽን አማካሪዋ ህዝበ ውሳኔው በተለያዩ ምክንያት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምፅ በማይሰጥባቸው 60 ያህል የምርጫ ክልሎች ጋር አንድ ላይ ጷጉሜ አንድ ቀን እንደሚካሄድ ነው አስታውቀዋል፡፡

(በደረሰ አማረ)