የ14 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ የ2023 የታዳጊ ተመራማሪዎች ሽልማት አሸናፊ ሆነ

መስከረም 30/2016 (አዲስ ዋልታ) በአሜሪካ የሚኖረው የ14 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሂመን በቀለ የ2023 የታዳጊ ተመራማሪዎችን ሽልማት አሸነፈ፡፡

ሂመን ሽልማቱን ያገኘው የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙና ፕሮጀክት በማቅረብና በሱ ደረጃ ካሉ ታዳጊ ተመራማሪዎች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ እንደሆነ ተመላክቷል።

ሂመን ውድድሩን በማሸነፉ የ25 ሺሕ ዶላር የተሸለመ ሲሆን ‘ከፍተኛ የአሜሪካ ታዳጊ ሳይንቲስት’ የሚል ማዕረግም ተሰጥቶታል፡፡

በቀጣይም በታላላቅ ተመራማሪዎች ስር ሆኖ ከፍተኛ ስልጠና የሚያገኝበት ዕድል እንደሚመቻችለትና ለቀጣይ ሳይንሳዊ ምርምሩም ሁለገብ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠርለት መገለጹን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ሂመን ባገኘው ድል የተሰማውን ደስታ በመግለጽ ሂመንን የመሳሰሉ በርካታ ታዳጊ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈጠሩ ወላጆችና የሚኖሩበት ማኅበረሰብ እያደረጉ ስላለው ጥረት አመስግኗል፡፡

ይኸው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አገልግሎቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡