የ150 ቢሊዮን ዩሮ የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ ሆነ

የካቲት 12/2014 (ዋልታ) በቤልጄም ብራሰልስ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረቶች የመሪዎች የጋራ ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ ስምምነት በደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ የጉባኤውን የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

ስምንት ነጥቦችን ባካተተው የጥምር ጉባኤው መግለጫ የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረቶች አጋርነታቸውን ለማደስና በጋራ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በርካታ ድንገተኛና ተደጋጋሚ ስጋቶች ሁለቱንም አኅጉራት የፈተኗቸውን ያህል ተስፋዎችም እንዳሉን ተረድተናል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

ለአኅጉራቱ አስተማማኝ ደኅንነት፣ ሰላም፣ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ብልጽግናን ለማምጣት በጋራ በመስራት የጋራ ራዕያቸውን እንደሚያሳኩም አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ ኅብረት የተዘጋጀውን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገውን የ2022 መልዕክት እንደሚደግፈውም ጠቅሷል።

በዓለም ዐቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት ላይ የታየው ኢፍትሐዊነት እንዲስተካከልና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆንም ሁለቱ ኅብረቶች በጋራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የአውሮፓ ኅብረትም እስከ 2022 አጋማሽ ድረስ 450 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ ክትባት ለአፍሪካ እንደሚሰጥ በጋራ መግለጫው አረጋግጧል።

425 ሚሊዮን ዩሮ በመመደብም የክትባት ምርትን ማፋጠን፣ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥና የባለመያዎች አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው የተባለው።

የአውሮፓ ኅብረትም በወረርሽኙ የተዳከመውን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የብድር ስምምነቶችን በመፈተሽ እስከ እዳ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ማረጋገጡን በመግለጫው ተጠቅሷል።

አጠቃላይ ዓለም ዐቀፋዊ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም አፋጣኝ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ሀገራት እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ የሚደረግ ሲሆን ከዚህም አፍሪካ በብዛት ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሏል።

በመግለጫው የጋራ እና ዘላቂ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትንሹ 150 ቢሊዮን ዩሮ የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ ተደርጓል።

ይህም የትምህርትና የጤና ዘርፍን ያካተተ ሲሆን የአውሮፓ-አፍሪካ የ2030 የጋራ ራዕይን እና አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንደሚያስችልም በመግለጫው ተብራርቷል።

በሁለቱ አኅጉራት መካከል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲኖር የሚሰራ ሲሆን በተለይም የአፍሪካ የነጻ ንግድና ገበያ ስርዓትን እውን ከማድረግ ባሻገርም ነባር የንግድ ስምምነቶችን በመፈተሽ ለቀጣይ የጋራ ሥራ የሚሆኑ ትብብሮች ይደረጋሉ ነው ያለው መግለጫው።

የሁለቱ አኅጉራት መሪዎች በሰላምና ደኅንነት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከርና ለማደስ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን የሚያጋጥሟቸውን ስጋቶች በጋራ ለመሻገርም አቅደዋል።

የአፍሪካ የስደተኞች ጉዳይ ተቋማትን አቅም በማጠናከር፣ የሀገራትን አቅም በመገንባት፣ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል በማካሄድ የሰዎች ህገወጥ ዝውውርና ስደትን ለመከላከል እንደሚሰሩም አቋም መያዛቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት በፀጥታው ምክር ቤትና ሌሎች ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ሁለቱም አኅጉራት በጋራ ይሰራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ፣ የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማፋጠን፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ፣ በሰላምና ደኅንነት አብሮ ለመስራት፣ ሁሉም የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል።