የ2015 አሸንዳ በዓል በሚሊኒየም አዳራሽ ነሐሴ 18 እንደሚከበር ተገለጸ

ነሐሴ 13/2015 (አዲስ ዋልታ) የ2015 የአሸንዳ በዓል በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ነሐሴ 18 ቀን 2015 እንደሚከበር የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪዎች ገለፁ።

በየዓመቱ የሚከበረው የአሸንዳ በዓል ባለፉት ዓመታት ተቀዛቅዞ ቆይቶ እንደነበር የገለጹት አስተባባሪዎቹ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እንደሚከበር ገልፀዋል።

 

ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት ኤፍሬም ኤርምያስ እንደገለፁት የዝግጅቱ ዋና ዓላማ የአሸንዳ በዓልን ባህላዊ ትውፊት ማስተዋወቅ ነው፡፡

በዚህም በበዓሉ ላይ ከ25 በላይ ታዋቂ የትግራይ አርቲስቶች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል፡፡

አስተባባሪው ጨምረውም ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ በትግራይ ውስጥ ለሚገኙ የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ እንደሚውል ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው የዝግጅቱ አስተባባሪ ዮሐንስ አርኣያ በበኩላቸው የአሸንዳ በዓል ባለቤቱ ህዝብ ነው ያሉ ሲሆን ከህዝብ በመጣልን ጥያቄ መሰረት ዝግጅቱ ከነሐሴ 16 ወደ ነሐሴ 18 2015 እንዲዘዋወር አድርገናል ብለዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲካሄድ የአዲስ አበባ መስተዳደር ልዩ እገዛ እንዳደረገም ተናግረዋል።

የአሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 24 የሚከበር ልዩ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።

በህይወት ዘርኡ