የ44 ቢሊዮን ዶላር የግዥ ስምምነትን ያፈረሱት ኤሎን መስክ በትዊተር ተከሰሱ

ኤሎን መስክ

ሐምሌ 6/2014 (ዋልታ) ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ትዊተር ከኤሎን መስክ ጋር ደርሶት የነበረው የሽያጭ ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደ።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ኤሎን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ደርሰው የነበር ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ስምምነቱን “አፍርሻለሁ” ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ ትዊተር ግዥውን በሕግ አስገድዶ ለማስፈጸም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል።

መስክ ስምምነቱን ለማፍረስ በምክንያትነት የጠቀሱት ትዊተር ምን ያክል ሐሰተኛ ተጠቃሚዎች እንዳሉት በቂ መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም የሚል ሲሆን ትዊተር ግን የተስማሙትን በአንድ የትዊተር የድርሻ ገበያ የሚከፈለውን 54̀.2 ዶላር መስክ እንዲፈጽሙ ፍርድ ቤትን ጠይቋል።

“ትዊተር ብዙ የሕዝብ መነጋገሪያ እንዲሆን በማድረግ የግዥ ፍላጎት አሳይተው ውልም ፈጽመዋል። ቢሆንም ግን መስክ ኩባንያውን ካከሰሩ፣ ሥራውን ካስተጓጎሉ፣ የባለድርሻዎችን ሃብት ዋጋ ቢስ ካደረጉ በኋላ ማንኛውም የውል ፈራሚ አካል ውሉን ለማቋረጥ ነጻ ነው ብለው ያምናሉ” ይላል ክሱ።

የትዊተር ሊቀ መንበር ብሬት ቴይለር “ኤሎን መስክ ለኮንትራት ግዴታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለን” በማለት ትዊተር ላይ አስፍረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

የክሱ ይዘት እንደሚያሳየው መስክ ከስምምነቱ ያፈገፈጉት “ለግል ፍላጎታቸው ስምምነቱ ከዚህ በኋላ ስለማይጠቅማቸው ነው” ብሏል።

መስክ የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሆናቸው ይታወቃል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW