ያለ ማስክ የሚደረግ እንቅስቃሴ ጠጥቶ እንደማሽከርከር ነው – ዶክተር ሊያ ታደሰ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ)- የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ በመሆኑ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።
የፌዴራል ፖሊስ በበኩሉ ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ሕጋዊ ቁጥጥሮችን ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚከናወኑ ሥራዎች አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ሊያ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በቫይረሱ የሚያዙ፣ ከተያዙም በኋላ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡና በቫይረሱ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።
ለአብነትም ባለፉት ስምንት ቀናት ብቻ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙና 119 ሰዎችም ለሕልፈት መዳረጋቸውን አስረድተዋል።
“ወደፅኑ ሕሙማን ክፍል የገቡ ሰዎች ቁጥር ከ600 ማለፉን ጠቅሰው እነዚህ አሃዞች ወረርሽኙ እየተጠናከረ መምጣቱን አመላካች ናቸው” ብለዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሚያሳየውን ቸልተኝነት በመቀነስና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ለቫይረሱ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ያለ ማስክ የሚደረግ እንቅስቃሴ መጠጥ ጠጥቶ እንደመንዳት ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ሊዘወተር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያውቁ ሰዎችም ራሳቸውን በአግባቡ በማግለል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ጎን ለጎንም የጽኑ ሕሙማን ክፍሎችን በአስፈላጊ ቁሳቁስ የሟሟላትና የማደራጀት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ መሆኑን ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቅድሚያ ኅብረተሰቡን የማስተማር ሥራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ጎን ለጎንም የሚወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ፖሊስ ሕጋዊ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ለዚህም በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የሚመራ ግብረ ሃይል መቋቋሙንና በቀጣይ ግብረ ሃይሉ የሚሰራቸውን ሥራዎች ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በማክበር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።