መጋቢት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ያሳለፍናቸው የፈተና ጊዜያት ምግባራችን እና ተግባራችንን መቅረጽ አለባቸው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
“ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት በመሻገር የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልእክት ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የምክክር እና ውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ፈታኝ፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስተማሪ የኾነ ውስብስብ ፈተናዎች ማስተናገዱን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግር ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከምንም በላይ ደግሞ ለአማራ ሕዝብ ነባር እሴት እና ማንነት የሚመጥን አልነበረም ብለዋል፡፡
በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የኅልውና አደጋ ተቀልብሶ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ዋጋ ለከፈሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው በአማራ ክልል ለተፈጠረው መጠነ ሰፊ ቀውስ ችግሮቹ ከውስጥም ከውጭም የሚመነጩ መሆናቸውን ገልጸው ያለፉት ወራት ለክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ፈታኝ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረው ጽንፈኛ ኃይል የደቀነውን አደጋ የክልሉ መንግሥት ለመቀልበስ የሄደበት ብስለት የተሞላበት መንገድ በበጎነት የሚጠቀስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የተከፈለው ዋጋ ውድ የሚባል ቢሆንም ክልሉን ከብተና መታደግ ተችሏል ያሉት ኃላፊው ችግሮችን መመርመር፣ ክፍተቶችን መለየት፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማመንጨት እና የቀጣይ ጊዜ ተግባራትን መንደፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የፖለቲካ አመራሩ ክልሉ የገጠመውን ውስብስብ ችግርና ፈተና በሚገባ ማጤን ይኖርበታል፤ አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት፣ ልምድ መቀያየር፣ መደጋገፍ እና መተጋገዝ ወቅቱ የፈጠረውን ፈተና ለመሻገር ምቹ መደላድል እንደሆነም ማስገንዘባቸውን የአሚኮ ዘገባ አመላክቷል።