ነሀሴ 24/2013 (ዋልታ) – ደቡብ ኮሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአምስት የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ድጋፍ የሚውል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር መለገሷን የአለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።
የአለም የምግብ ፕሮግራም ከደቡብ ኮሪያ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ ፣ማዳጋስካር ፣ደቡብ ሱዳንና ቡርኪናፋሶ ተረጂዎች ሰብአዊ እገዛ ይውላል ብሏል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም የምእራብ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ በቡርኪናፋሶና በናይጄሪያ እርዳታ ጠያቂዎች ስም ከደቡብ ኮሪያ ህዝብና መንግስት ለተደረገልን ወቅቱን የጠበቀ ልገሳ እናመሰግናለን ብለዋል።
በአየር ንብረት መለወጥ ፣በኮቪድ 19 መስፋፋትና በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አለመኖር ምክንያት የማዳጋስካር ተወላጆች ከፍተኛ የምግብ እጥረትና የምግብ ዋስትና ማጣት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም የደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር መንግስተአብ ሃይሌ ሰዎች ለርሃብ እንዳይጋለጡ ስጋት እንዳለ ገልጸዋል።
ከኮሪያ ህዝብና መንግስት የተገኘው ልገሳ ወቅቱን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም በግጭት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በአየር ንብረት መለወጥ እና በተለያዩ ምክንያቶች የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ተጎጂዎች ለሚያደርገው ድጋፍ በፈረንጆቹ በ2020 የሰላም ኖቤል ሽልማትን ማግኘቱ ይታወሳል።