ዲያስፖራው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል ተባለ

ጥር 2/2014 (ዋልታ) ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በኅልውና ትግል ላይ መሆኗን በማሰብ ለአገራዊ ዘላቂ ጥቅም በትጋት እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጄንሲ ጠየቀ፡፡
ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዲያስፖራ ጥምረት በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ላይ ከዲያስፖራ ማኅበረሰብ ስለሚጠበቁ እንቅስቃሴዎች ውይይት አካሂዷል።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ አካል ነው ያሉ ሲሆን በአገር ቤት ያለው ሕዝብ ተስፋ እና ስጋቶች የዲያስፖራውም ተስፋና ስጋቶች ናቸው ብለዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች በኅልውና ትግሉ ወቅት ከፍተኛ የዜጋ ዲፕሎማሲን ያበረከተ እና ኢትዮጵያ ያለባትን የዲፕሎማሲ ክፍተቶች ያሟላ ሚና ነበረው ብለዋል።
በሀብት ማሰባሰብ ረገድም ዳያስፖራው ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች እና ለአገራዊ ፕሮጀክቶች ገንዘቡን እየለገሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ዳያስፖራው ካለው አቅምና ፍላጎት አንፃር አሁንም ብዙ መስራት የሚጠበቅብን ነገሮች አሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።