ዲፕሎማቶች በየተመደቡበት ተልዕኮ ለስኬት እንዲተጉ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ አሳሰቡ

ሁሉም ዲፕሎማት አገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በንቃት በመገንዘብ በየተመደበበት ተልዕኮ ለስኬት መትጋት እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

ሚኒስትሩ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ተጠሪ ተቋማት በተዘጋጀው ሁለተኛው ዙር ስልጠና ላይ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን አዎንታዊ ገፅታ ለማስፋት ዋናው መስሪያ ቤትን ከማጠናከር ጀምሮ ኤምባሲዎችን እና ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶችን የማደራጀት ሥራ ይከናወናል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከውስጥም ከውጭም የተደቀነውን ፈተና ለመቀልበስ በትብብር እና በመናበብ የሚራመዱበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ዛሬ በተጀመረው ስልጠና ተሳታፊ የሆኑ የሁለተኛው ዙር ሰልጣኞች በአገሪቱ ውስጥ እየተካሔደ ያለውን ዘርፈ ብዙ የተቋማት ማሻሻያዎች እና አደረጃጀቶችን በማጤን እኔ ለሀገሬ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ምን ሠራሁ በማለት ራሳቸውን መጠየቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ማሻሻያ እና ክለሳ በማጠናቀቅ የመጨረሻውን ግብዓት እየሰበሰበ መሆኑን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳቱ እና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ በመሆናቸው በአገራችን ጥቅም ላይ ጥላ እንዳያጠላ የመቀልበስ እና አዎንታዊ መረጃዎችን የማስፋት ስራም መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።