ዳሽን ቢራ እና ፋሲል ከነማ ውላቸውን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አራዘሙ

ዳሽን ቢራ እና ፋሲል ከነማ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) ዳሽን ቢራ እና ፋሲል ከነማ ውላቸውን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ማራዘሙን አስታወቁ፡፡

የ2013 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለድል ፋሲል ከነማ ላለፉት ዓመታት ዋና አጋሩ ከሆነው ዳሽን ቢራ ጋር ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የ136 ሚሊየን ብር ስምምነት ውል በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ተፈራርሟል፡፡

ፋብሪካው ክለቡ ዘንድሮ በሊጉ አንደኛ ከወጣ 2 ሚሊዮን፣ ሁለተኛ ከሆኑ 1 ሚሊዮን ብር ጉርሻ እንደሚሰጥና የገቢ ማሰባሰቢያ ብሎ በሚያዘጋጀው ኮንሰርት ሩጫና ሌሎች ፕሮግራሞች ላይም ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ዳሽን ቢራ ባለፉት 20 ዓመታት በኅብረተሰብ ዐቀፍ አስተዋጽኦ ወደ 800 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉም ተጠቅሷል።

የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አብርሃም ዘሪሁን ፋሲልን መደገፍ ማኅበረሰቡን መደገፍና ሻምፒዮን ሲሆን እኛም ሻምፒዮን እንዳደረገን መታሰብ አለበት” በፊርማ ሥነሥርዓት ወቅት አስረድተዋል።

የክለቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቢዮት ብርሃኑ በበኩላቸው በውሉ ደስተኞች ነን፤ ከፋሲል ከነማ ስኬት ጀርባ ዳሽን ቢራ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ በክለቡና በደጋፊዎቻችን ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

በደግነት መኩሪያ