አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ

ኃይሌ ጉርሜሳ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) በቄለምና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው ሌሎች አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች አርሶ አደሮችንና ሌሎች ሰላማዊ ወገኖችን ጭምር በመግደል፣ በመዝረፍና በማገት አሸባሪው ሸኔ በሕዝብ ላይ የከፋ ችግር እያደረሰ ይገኛል።

በመሆኑም አሸባሪ ቡድኑን ለማጥፋት ከሕዝብና የተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኃይሌ ጉርሜሳ ገልጸዋል።

ኃላፊው በቄለምና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም ሌሎች አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው በዚህም የሽብር ቡድኑ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በጸጥታ ኃይሉ እየተወሰደ ያለው የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏልም ብለዋል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች አሸባሪው ሸኔ የፀጥታ ችግር እየፈጠረ እንደሆነና የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት እየተወሰደ ባለው እርምጃ በአንዳንድ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋና ምዕራብ ሸዋ አካባቢም አሸባሪው ሸኔ በሰዎች ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል መፈፀሙን አስታውሰው በአሸባሪው ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ገልጸዋል።

“በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም በወለጋ ዞኖች የሸኔ የሽብር ቡድን እየተደመሰሰ ነው” ያሉት ኃላፊው በቄለም ወለጋ አካባቢ በሁለት ወረዳዎች በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ አካባቢው ከሽብር ቡድኑ ነጻ መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ጉጂ አካባቢም በአሸባሪው ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዶበት ከሽብር ቡድኑ አካባቢው ነጻ ሆኗል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሀገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ሕዝቡ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።