ዳሽን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

የካቲት 17 / 2013 (ዋልታ) – ዳሽን ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ባንኩ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ከነገ ጀምሮ ለስድስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር አስታውቋል።

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ እንዳሉት፤ ባንኩ በየዓመቱ ከሚያገኘው ትርፍ ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ ያላቸውን ተቋማትና ግለሰቦችን ሲደግፍ ቆይቷል።

ባንኩ ለገበታ ለአገር 30 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለገበታ ለሸገር ደግሞ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን በማሳያነት ገልጸዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በተጨማሪም ለኩላሊት እና ልብ ህሙማን ድጋፍ ማድረጉን የጠቆሙት አቶ አስፋው፤ “በቀጣይም ዳሽን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

ባንኩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደስራ ለማስገባትና በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ባንኮች ተርታ ለመሰለፍ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዳሸን ባንክ ከ450 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚልቁ ደንበኞችን ማፍራቱም ገልጿል፡፡