ግንቦት 24/2013 (ዋልታ) – “ድምጻችን ለነጻነታችን” በሚል በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ፡፡
በሰልፉ ላይ የተገኙ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ ሀገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጀመረችውን የለውጥ አስተሳሰብ እና ሁሉ አቀፍ ልማት በሴረኞች ፖለቲካ አይደናቀፍም ብለዋል፡፡
ዜጎች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ በመሆን ለሀገር ያላቸውን ውግንና መግለጽ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ጎደቶ በበኩላቸው፣ ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማደናቀፍ የተነሱ አሸባሪዎች እና የውጪ አገራት ጣልቃ ገብነት ተገቢ አለመሆኑን ለመቃወም የሚደረገውን ድጋፍ በተሳተፍንበት በማናቸውም አጋጣሚ መግለጽ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ በሰልፉ የተለያዩ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን፣ ዓባይ የኔ ነው፣ እኛ የአገራችንን ሉዓላዊነት እናስከብራለን፣ በአገራችን ጉዳይ የኃያላኑን አገራት ጣልቃ ገብነትን እንቃወማለን እና ተመሳሳይ መልዕክቶችን አሰምተዋል።
ለደሬቴድ አስተያየታቸውን የሰጡት የሰልፉ ተሳታፊዎችም አባቶቻችን በመስዋዕትነት ያቆዩልንን ሀገራችንን እኛ ለቀጣይ ትውልድ እናስረክባለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሰልፉ ላይ በዞኑ ከተለያዩ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች፣ ከታርጫ ከተማ አስተዳደር እና ከታርጫ ዙሪያ ወረዳ የመጡ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።