ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በመሆን ተሾሙ

የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አድርጎ መሾሙን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቅርቡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ለሚፈልጉ ሁሉ በመገናኛ ብዙኃን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ስምንት ተወዳደሪዎች ቀርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከተወዳዳሪዎቹ መካከልም ዶክተር አህመድ የዩኒቨርሲቲውን ሴኔት ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ነው ቀጣዩ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙት፡፡

ሚኒስቴሩ ከፍተኛ አደራና ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን በማሳሰብ ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡም አሳስቧል፡፡

ዶክተር አህመድ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንትነት በኋላም ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 14 ዓመታት ሲያገለግሉ መቆየታቸውም ተጠቁሟል፡፡