የአድዋ ድል በዓል በደቡብ ክልል በድምቀት እየተከበረ ነው

የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – 125ኛው የአድዋ ድል በዓል በክልል ደረጃ በወላይታ ሶዶ ከተማ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና አርበኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በተገኙበት ነው እየተከበረ የሚገኝው::

በበዓሉ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ አድዋ የህብረብሔራዊነታችን አርማ የድል አድራጊነታችን ማሳያ የሆነ በመሳሪያ ሳይሆን በአእምሮ ልዕልና ማሸነፍ የቻልንበት ኩራታችን የሆነ ልዩ በዓላችን ነው ብለዋል።

በአሉን የምናከብረው እንዲሁ ሠማአታቱን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን የድሉን ተምሳሌት ወስደን በዛሬው ኑሮአችንም የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለማሸነፍ የምንጠቀምበት ሊሆን ይገባልም ሲሉ አክለዋል።

የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ በበኩላቸው አድዋ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት እና አልበገር ባይነትን የሚያሳይ የህዝቦች አንድነት ያመጣው አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል።

በዓሉ በደቡብ ክልል ደረጃ የታታሪነት እና የህብረብሔራዊነት መገለጫ በሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ መከበሩ አንድም ቀን በኢትዮጵያዊነቱ ለማይደራደረው የወላይታ ህዝብ ደስታን ፈጥሮአል ሲሉ የገለፁት የዞኑ አስተዳደሪ በአድዋ ጦርነት የወላይታ ህዝብም መስዋትነት መክፈሉንም ጠቁመዋል፡፡

ዛሬም በሀገር ጉዳይ አድነታችንን አጠናክረን ከየትኛውም ችግር ልናላቅቃት እንደ አድዋ ሁሉ ያለምንም ልዩነት ልንረባረብ ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።

በዓሉ በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ መሠናዶዎች ደምቆ እየተከበረ ሲሆን የበዓሉን ታሪካዊ ዳራ የሚዘክር ጥናታዊ ፅሁፍም ቀርቦአል።

(በድልአብ ለማ)