ጃፓን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አራዘመች

ሚያዚያ 29/2013 (ዋልታ) – የቶኪዮ የኦሎምፒክ ውድድር ሊጀመር ከ3 ወራት በታች በቀረበት በዚህ ወቅት ጃፓን ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ጥላው የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የእንቅስቃሴ ገደብ ማራዘሟ ተዘገበ፡፡

ቀደም ሲል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸው የነበሩት የቶኪዮ፣ የኦሳካ፣ የሀዮጎ እና የኪዮቶ ከተሞች ገደቡ የሚያበቃው እኤአ ግንቦት 11 የነበረ ሲሆን አዋጁ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ እንዲራዘም ማድረጓ ነው የተዘገበው፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ ቀደም ሲል ገደብ ከተጣለባቸው ከተሞች በተጨማሪ አይቺ እና ፉኩኦካ የተባሉ የሀገሪቱ ግዛቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንዲካተቱ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ መስፋፋቱና መሰል የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸው ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እና ዕቅድ ስለመከናወኑ ጥርጣሬ ማጫሩም በዘገባው ተመላክቷል፡፡

በሀገሪቱ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ምግብ እና መጠጥ ቤቶች የአልኮል መጠጦችን እንዳይሸጡ ወይም ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ የተደረገ ሲሆን ቲያትር እና ሌሎች መዝናኛ ቤቶች ደግሞ እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡

በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይ አሁንም በኮሮና ቫይረስ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሆስፒታሎችም እየሞሉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት አራተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበል እንዳይከሰት ለማድረግ አጭርና ፈጣን ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊደነገግ እንደሚችል መናገራቸውም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡