የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ዛሬ ይመረቃል

ሚያዝያ 30/2013 (ዋልታ) – የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ምዕራፍ አንድ የሞጆ – መቂ – ባቱ መንገድ ዛሬ ይመረቃል።
የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በሁለት ምዕራፍ እና በአራት ኮንትራት የተከፈለ ነው፡፡ የምዕራፍ አንድ የሞጆ – መቂ- ባቱ ኮንትራት አንድ ፣ የሞጆ – መቂ እና ኮንትራት ሁለት የመቂ – ባቱ 92 ኪ.ሜ. መንገዶች ግንባታ ስራ ተጠናቆ ዛሬ
ይመረቃል፡፡
የፍጥነት መንገዱ 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 92 ኪ.ሜ ርዝመት ሲኖረው እያንዳንዱ የተሽከርካሪ መጓጓዣ መስመር 3 ነጥብ 65 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ሲሆን የመንገድ አካፋይ (ሜዲያን) ስፋቱ 9 ሜትር ነው፡፡
የግንባታው የገንዘብ መጠን 6.3 ቢሊየን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
የመንገድ አካፋዩ በዚህ ደረጃ እንዲሰፋ የተደረገው በተቃራኒ አቅጣጫ ያለን ተሽከርካሪን በመለየት አደጋን ለማስወገድ አልያም ለመቀነስ እንዲሁም በቀጣይ መንገዱን ማስፋት ካስፈለገ ያለተጨማሪ የወሰን ማስከበር ሥራ በቀላሉ ለማስፋፋት መሆኑ ታውቋል።
የመንገዱ ትከሻ ስፋት ከ1 ነጥብ 75 ሜትር እስከ 2 ነጥብ 25 ሜትር የያዘ ሲሆን በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን ያስተናግዳል ተብሏል፡፡
የመንገዱ አጠቃላይ ወሰን ስፋት 90 ሜትር ነው። ይህም በቀጣይ ለሚኖረው የማስፋፋት ስራ በቂ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ይሆናል፡፡
በተጨማሪም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ ከሞጆ እስከ ሃዋሳ ባለው የመንገዱ መስመር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አካባቢውን የማስዋብ ስራ ተጀምሯል፡፡
በፍጥነት መንገዱ ለመጠቀም የተቀመጠለት የፍጥነት ገደብም በሰአት ከ80 እስከ 120 ኪ.ሜ. መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፍጥትነት መንገዱ በተመረጡ ቦታዎች የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መረጃ የሚሠጡ ካሜራ እና ሌሎች የፍጥነት
መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች የሚኖራቸው ይሆናል፡፡
የዚህ ቀጣይ ክፍል የሆነው የምዕራፍ ሁለት ባቱ – አርሲነገሌ – ሀዋሳ፣ ኮንትራት ሶስት ባቱ – አርሲነገሌ እና ኮንትራት አራት አርሲ ነገሌ – ሀዋሳ 110 ኪ.ሜመንገዶች ግንባታ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
(በደረሰ አማረ)