ጆ ባይደን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተሳሳቱ የኮቪድ-19 መረጃዎች ሰዎችን ለሞት እየዳረጉ መሆናቸውን ገለጹ

ጆ ባይደን

ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተሳሳቱ የኮቪድ-19 መረጃዎች ሰዎችን ለሞት እየዳረጉ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለኮቪድ ክትባት እና ስለወረርሽኙ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆናቸውን በተመለከተ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ዋይት ሐውስ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመከላከል በማኅበራዊ ሚዲያ ድርጅቶች ላይ የሚያሳድረውን ጫና እየጨመረ ነው።

አርብ ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ባይደን “ሐሰተኛ መረጃዎች ሰዎችን እየገደሉ ነው” ያሉ ሲሆን፣ “አሁን ወረርሽኙ ያለው ባልተከተቡ ሰዎች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናትም በአገሪቷ አሁን ላይ ያለው የኮቪድ-19 ሞት እና ሥርጭት ነጥሎ እያጠቃ ያለው ያልተከተቡ ማኅበረሰቦችን እንደሆነ አሳስበዋል።

ከአርብ ዕለት ቀደም ብሎ የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ ፌስቡክና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች ስለ ክትባት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ቀደም ብለው ማስቆም አልቻሉም ሲሉ ወቅሰዋል።

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ኬቪን ማክአሊስተር በበኩላቸው፣ “ድርጅቱ በሚቀርብበት በመረጃ ያልተደገፉ ክሶች አይረበሽም” ብለዋል።

ድርጅቱ የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

 

ድርጅቱ ባወጣው ሌላ መግለጫ ላይም እስካሁን ከ18 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ኮቪድን የተመለከቱ የተሳሳቱ መረጃዎችንና የፌስቡክን ሕግ የጣሱ ገጾችን ማስወገዱን እንዳሳወቀ ቢቢሲ ዘግቧል።