ገዳ ባንክ የዋና መስሪያ ቤቱን ሕንፃ በይፋ አስመረቀ

ገዳ ባንክ የዋና መስሪያ ቤቱ

ታኅሣሥ 15/2015 (ዋልታ) የገዳ ባንክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የዋና መስሪያ ቤቱን ሕንፃ በይፋ አስመረቀ።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ(ዶ/ር) ገዳ ባንክ ትልቅ ስምን ይዞ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው በሀገሪቱ ነባርም ይሁኑ አዳዲስ ባንኮች ኢኮኖሚውን በመደገፉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ቁጠባ ላይ ርብርብን በማድረግ ባንኩን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ እና በገጠር ላለው ክፍለ ኢኮኖሚ በይበልጥ በመንቀሳቀስ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የገዳ ባንክ ፕሬዝዳንት ወልዴ ቡልቱ በበኩላቸው ባንኩ ዘመኑ ባለበት የቴክኖሎጂ ደረጃ 30 በሚሆኑ ቅርንጫፎች ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸው በ300 ሰራተኞች ስራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ካሉ ባንኮች ጋር በጥምረት እንደሚሰራ የገለጸው ባንኩ የተለያዩ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የባንኩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ወደ ስራ መግባቱንም አመልክቷል፡፡

ባንኩ ከ28 ሺሕ በሚበልጡ ባለአክሲዮኖችና በ552 ሚሊየን የተከፈለ ካፒታል እንዲሁም የተፈረመ 1 ነጥብ 167 ቢሊየን ካፒታል ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።

በግዛቸው ይገረሙ