ግብፅ 13 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመች

ነሐሴ 09/ 2014 (ዋልታ) የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ የውሃና መስኖ ሚኒስትሩን ጨምሮ 13 አዲስ የካቢኔ አባላት ሹም ሸር እዲደረግላቸ ለሀገሪቱ ፓርላማ ያቀረቡትን ፀደቀ።

ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር በአገሪቱ የካቢኔ አባላት ላይ ከፍተኛ የተባለውን ለውጥ ለማድረግ በእረፍት ላይ የነበረው ፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደረግ የጠየቁት ባለፈው አርብ ነበር።  አብዛኞቹ የሀገሪቱ ሚኒስትሮች በአዲስ የተተኩበት  ካቢኔ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ትላንት  ጸድቋል።

በአዲሱ የግብፅ ካቢኔ ውስጥ ዋነኛ የሚባሉት የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትርን ጨምሮ 13 ሚኒስትሮች በአዲስ ሲተኩ፣ የገንዘብ፣ የመከላከያ፣ የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቦታቸው ቀጥለዋል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በሚኒስተሮቻቸው ላይ ለውጥ ያስፈለገበትን ምክንያት በማኅበራዊ ሚዲያ እንደገለጹት “በአገር ውስጥና በውጪ የአገሪቱን ጥቅም በማስጠበቅና ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ በማጎልበት የመንግሥትን የአፈጻጸም ብቃት ለማጠናከር ነው” ብለዋል።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሥራውን ለመጀመር ለሦስት ወራት ዕረፍት ተዘግቶ የነበረው የግብፅ ፓርላማ አባላትም “ለአስቸኳይ ጉዳይ” በሚል ቅዳሜ እንዲሰበሰቡ ተጠርተው አዲስ የቀረቡትን ሚኒስትሮች ሹመት ትላንት አጽድቋል። ተሿሚዎቹ ሚኒስትሮች ሥራ ለመጀመር በፕሬዝዳንቱ ፊት ትላንት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

የግብፅን የመስኖ እና ውሃ ሚኒስትርነት ቦታን የተረከቡት አዲሱ ተሿሚ ሃኒ ሴዊላም ሲሆኑ፣ አዲሱ ሚኒስትር በዘርፉ ሦስት አስርት ዓመታት የሚጠጋ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ መሆናቸው ይነገራል።

መንግሥታዊው አል አህራም እንዳለው አዲሱ የግብፅ የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትር የሚጠብቃቸው ቀዳሚ ሥራ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ይሆናል።