ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ደረጃ በደብረ ማርቆስ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር አስጀመሩ

                                                  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ግንቦት 30/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ደረጃ በደብረ ማርቆስ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር አስጀመሩ፡፡

ኢትዮጵያን እናልብስ በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው 3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማ በዛሬው ዕለት የተጀመረ ሲሆን፣ በማስጀመሪያ መርኃግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁም የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በአማራ ክልል በዘንድሮው ዓመት 1 ነጥብ 83 ቢሊየን  ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣ ሀምሌ 8 ቀን በእንድ ጀንበር ከ247 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ መያዙን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ ለዋልታ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በአንድ ጀንበር በ2011 ዓ.ም 75 ሚሊየን ችግኝ ሲተከል በ2012 ዓ.ም ደግሞ 290 ሚሊየን ችግኝ ተተክሏል። ይህም በክልሉ ከ35 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በደን እንዲሸፈን አስችሏል ነው የተባለው።

በዘንድሮው መርሃ ግብርም ለምግብነት የሚውሉና ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ አገር በቀል ተክሎችን ለመትከል ነው ዝግጅት የተደረገው።

በክልሉ የተተከሉና የሚተከሉ ችግኞች መጠንና ያሉበትን የጽድቀት ሁኔታ በቀላሉ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱንም አቶ ማርቆስ ተናግረዋል።

በዓባይ ወንዝ ከሀገር ከሚተመው ለም አፈር 60 በመቶ የሚሆነው ከክልሉ የሚወጣ ሲሆን፣ ይህን ለማስቀረት ለችግኝ ተከላ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ተብሏል።

በዘንድሮው ዓመት በሚተከለው የችግኝ ተከላ መርኃግብር የጎረቤት ሀገራትን ለማሳተፍ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።

(በአስታርቃቸው ወልዴ)