መጋቢት 27/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኮቪድ19ኝን ለመከላከል እና የህዝቡን ጤንነት ለመጠበቅ ከወጣው መመሪያ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ሙሉ ማብራሪያው እንደሚከተለው ቀርቧል
- ስለ ስብሰባ፤ ስለ ስብሰባ የሚደነግገው አንቀጽ ውይይት ማድረግ የሚፈልግ የትኛውም ተቋም የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከ50 እንዳይበልጥ የሚከለክል ሲሆን ከ50 በላይ ተሳታፊዎችን የሚያቅፉ ውይይቶች አስገዳጅ ሲሆኑ የአዳራሹን ወይም የመወያያውን ስፍራ ሰው የመያዝ አቅም አንድ አራተኛውን በመጠቀም እና ለሰላም ሚኒስቴር በማሳወቅ እንዲሁም በተሳታፊዎቹ መካከል የሚኖረው አካላዊ ርቀት ከሁለት የአዋቂ እርምጃ ሳያንስ እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀሙ እና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረግ ማከናወን የሚቻል መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ከዚህ እና መመሪያው ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ድርጊትን የሚከለክሉ ሳይሆኑ ገደብ የሚጥሉ በመሆናቸው ገደቦቹን በማክበር የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ህግ ነው፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ እና መሰል የህዝብ ስብሰባዎች አካሄድ ላይ ገዢውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን መመሪያ ባከበረ ሁኔታ መከወን አለባቸው፡፡
ከዚህ በዘለለ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ወይም ህዝቡን አግኝተው ዓላማቸውን መግለጽ መቻላቸው ለፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን ለመራጩ ህዝብ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ለማካሄድ የሚረዳው በመሆኑ የምርጫ ቅስቀሳ እና ውይይቶች መደረጋቸው የሚፈለግ ነውና የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን በማክበር መንቀሳቀስ በህግ የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡
- ሌላው ከላይ የተጠቀሰውን የምርጫ ቅስቀሳ እና ውይይት ለማድረግ የፈለገ አካል ወይም ፓርቲ ስብሰባውን ለማድረግ ፈቃድ የሚጠይቀው አካል አለመኖሩ ነው፡፡ በዚህ መመሪያ መሰረት የኮቪድ 19ን ስርጭት ለመከላከል የተቀመጡትን ገደቦች እስካልጣሰ ድረስ ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ ከየትኛውም የመንግስት አካል ፈቃድ እንዲሰጠው የመጠየቅ ግዴታ የሌለበት ሲሆን የሰላም ሚኒስቴር የተጣለበትን በሽታውን የመዋጋት ኃላፊነት በሚገባ መወጣት እንዲችል ስብሰባው እንደሚደረግ አስቀድሞ ሚኒስቴሩ እንዲያውቅ ማድረግ ግን ግዴታ ነው፡፡
- መመሪያው በመንግስት ተቋማት ላይም ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑ፤ ለቋማችን እየቀረቡ ካሉት ጥያቄዎች መካከል አንዱ መመሪያው በመንግስት ተቋማት ቢጣስ ተጠያቂነትን ያስከትላል ወይ የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከመመሪያው የምንረዳው የወጣበት ዓላማ ሁሉንም የማህበረሰብ አካል በእኩል ለመግዛት ነው፡፡
ይህ ማለት በመመሪያው የተጣሉትን ገደቦችም ሆነ ግዴታዎች ጥሶ የሚገኝ ማንኛውም የመንግስት ተቋም እንደ የግል ተቋማት እና ግለሰቦች ሁሉ በህግ ከመጠየቅ የሚድንበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው፡፡
የመንግስት ተቋማት ግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች በህጉ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ምሳሌ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡ ቀድመው የታቀዱ ውይይቶቻቸውን እየሰረዙ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ እያራዘሙ ወይም በበየነመረብ ለማካሄድ በመወሰን ላይ ላሉ ተቋማት ኮሚቴው ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
- ስለ ቅጣት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ካለው በቀላሉ የመሰራጨት ዕድል የተነሳ ሰዎችን ማሰር አማራጭ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ወደ እስር ከመገባቱ በፊት ህዝቡን ማስተማር እና ማስጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ትምህርቱን እና መስጠንቀቂያውን ችላ ብለው በወንጀል ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችን በወንጀል መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ መመሪያው ያመላከተው የወንጀል ህጉም አንቀጽ 522 በድርጊቱ ጥፋተኛ የተባለ ሰው እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡ ይህ ማለት አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ማስክ አለማድረግ 2 ዓመት ያስቀጣል በሚል መረዳት አደጋ አለው፡፡
ድንጋጌው ቀላል እስራቱ እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ነው የሚለው፤ እስከ ከተባለ 2 ዓመት ጣራው ሆኖ መነሻ የእስራት መጠን አለው ማለት ነው፡፡ በወንጀል ህጋችን ጠቅላላ ክፍል ቀላል እስራት መነሻው 10 ቀን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ወንጀሉ የሚያስጠይቀው በ2 ዓመት ሳይሆን ከ10 ቀን እስከ 2 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጸመ የተባለው የህግ ጥሰት ውስጥ ያሉ የድርጊት እና የሀሳብ ክፍል ከግምት ገብቶ እንደ ወንጀሉ ክብደት ደረጃ ወጥቶለት የሚወሰን ነው ማለት ነው፡፡
በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት አንድ አጠገቡ ካለ ሰው ከ2 ሜትር በታች በሆነ ርቀት ውስጥ ተጠግቶ የቆመ ሰው እና በሽታው እንዳለበት እያወቀ ከሌሎች ጋር የተቀላቀለ፤ አብሮ የተንቀሳቀሰ ወይም ምግብ የተመገበ ሰው የወንጀል ባህሪ (አደገኝነታቸው) እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ሰው መቀጣት ያለበት ባጠፋው ልክ በመሆኑ ቅጣት ሲጣል ይህንን ከግምት የሚያስገባ ይሆናል፡፡