ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ከፕሬዝዳንት ፌሌክስ ሲሽኬዲ ጋር ተወያዩ

ግንቦት 03/2013 (ዋልታ) – የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፌሌክስ ሲሽኬዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሲሽኬዲን እና የልዑካን ቡድናቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተቀብለዋቸዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው ውይይትም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች በመፈለግ፣ እንዲሁም በአሁኑ የህብረቱ ሊቀመንበር አመቻችነት በአፍሪካ ህብረት በሚመራው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የድርድር ሂደት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

አክለውም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል የትብብር እና የጋራ ልማት ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል እና በሁለቱም ሀገራት ላይ ጉዳት በማያስከትል መንገድ እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ አቋም አስረድተዋል፡፡

በትብብር መርህ ማህቀፍ (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) መሠረት ለሁሉም ወገኖች የሚጠቅም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያላትን ፍላጎት ኢትዮጵያ ደግማ ትገልጻለች ተብሏል፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፌሊክስ ሲሽኬዲ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከማድረጋቸው አስቀድሞ ከግብጽና ሱዳን ጋር በድርድሩ ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል፡፡

(በአስታርቃቸው ወልዴ)