ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

ሰኔ 26/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል ለሆነው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ገበታ ለሸገር’ እና ‘ገበታ ለሀገር’ የቱሪዝም ሴክተር ልማት ሥራዎች በአብዛኛው መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ይሄን ተከትሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት የ‘ገበታ ለትውልድ’ ሐሳባችንን ገፍተንበታል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን በ120 ሄክታር መሬት ላይ የአባያ ሐይቅን እያየ በሚያማምር ቦታ ላይ እንዲገነባ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚሸፍነውን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ ገቢን ተቋዳሽ እንድንሆን ያደርገናል ሲሉም አክለዋል።

ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብታችንን በመጠቀም ሀብት የማፍራት ጅምሮችን በማስፋፋት፣ የብልጽግና ጉዟችንን ለማሳካት እንተጋለንም ብለዋል፡፡