ጥቅምት 1/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2015 በጀት ዓመት የግብር ከፋዮች ዕውቅና አሰጣጥ መርኃ ግብር ላይ በመገኘት በታማኝነት ብሔራዊ ግዴታቸውን የተወጡ ግብር ከፋዮችን ሸልመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና ማኅበረሰቡ የገቢ መሰረትን የሚያሳዳጉ ስራዎችን እንዲደግፉ አሳስበው ሌብነትን፣ ኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥነትን ማስወገድ፣ ስርዓትን እና ተገማችነትን ማካተት እንደሚገባ አንስተዋል::
መንግስት የግብር አከፋፈል ስርዓቱን እና አሰራሩን ማዘመን ሲኖርበት የግሉ ሴክተርም መሳ ለመሳ በቴክኖሎጂ መዘመን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
በ2015 በጀት ዓመት ጥቅል የገቢ እቅድ 450 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን ክንውኑ 442 ቢሊዮን ሆኖ መጠናቀቁም ተመላክቷል።
ከዚህ ውስጥ በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ ግብር የተሰበሰበው 264.35 ቢሊዮን ብር እንደነበርም ተገልጿል።
በዛሬው መርኃግብር ላይ በአጠቃላይ 500 ግብር ከፋዮች እውቅና እንደተሰጣቸውም ተጠቁሟል።