የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

ጥቅምት 1/2016 (አዲስ ዋልታ) የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ”ኤር ናይጄሪያ” የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን 49 በመቶ ድርሻ ይዞ ለማቋቋም በቂ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱና ይህንን ተከትሎ አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግሥትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጄሪያ ባለኃብቶች ጋር ሥምምነቶች መፈረማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የናይጄሪያን ብሔራዊ አየር መንገድ በጋራ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በቅርቡ በናይጄሪያ አዲስ መንግሥት መዋቀሩን ተከትሎ አየር መንገዱን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ናይጄሪያ አቡጃ በማቅናት ከናይጄሪያ መንግሥት ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

በወይይቱም የናይጄሪያ የመንግሥት አካላት ስለ ብሔራዊ አየር መንገዱ መቋቋም የፕሮጀክት ሂደት ለማወቅ ጥቂት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ‘እየጠበቅናቸው ነው” ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።